የሕክምና ባለሙያዎች ሥራ ማቆም አድማ ከሕግና ከስነ-ምግባር ያለዉ አንድምታ! ሕሊና ፈረደ እና ጤናዳም

ይህን ጦማር ለመጻፍ የተነሳነዉ ከሰሞኑን የሕክምና ባለሙያዎች ሥራ ማቆም አድማ ጋር በተገናኘ አድማዉን በመደገፍና አለመደገፍ የሃሳብ ልዩነቶች ሲንፀባረቁ በመመልከታችን ነዉ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ያነሱት ጥያቄ እኛም የምንደግፈዉ ነዉ፡፡ ሆኖም ሥራ ማቆም አድማዉን በተመለከተ ከስሜታዊነትና ጀብደኝነት ወጥተን ነገሩን ከስሩ መመልከት ይሻላል በሚል ጽሁፉን አዘጋጅተናል፡፡ ጽሁፉ ከመማማርና መረጃ ከመለዋወጥ ያለፈ ዓላማ የለዉም፡፡ የማንንም ጥያቄና አጀንዳ እንዲያኳስስ ተብሎም የቀረበም አይደለም፡፡ ጽሁፉ ቢረዝምም መልካም ንባብ!
——–
የስራ ማቆም አድማ!

በታሪክ የመጀመሪያዉ የስራ ማቆም አድማ ሆኖ የተመዘገበዉ በ12th century BC በድሮዋ ምስር አገር (በአሁኗ ግብፅ) በንጉስ ራምሴ ሶስተኛ ዘመን መንግስት የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ለሰሩበት ምንዳ ባለማግኘታቸዉና በነበረዉ የነቀዘ/ሙሰኛ አሰራር ምክንያት በሚደርሳባቸዉ በደል ምክንያት ያደረጉት የስራ ማቆም አድማ ነበር፡፡ በተለያዩ የዓለማችን ክፍል ተከታታይ የስራ ማቆም አድማዎችም ተደርገዋል፡፡ እስካሁንም እየተደረጉም ይገኛል፡፡ የስራ ማቆም አድማ ሰራተኞች አሰሪያቸዉን አስገድደዉ ወደ ድርድር የሚያቀርቡበት ፈርጣማ ክንዳቸዉም ሆኗል፡፡ የስራ ማቆም አድማ እንደ ሁኔታዎችና እንደሚተገበርበት ዘርፍ በተለያዬ መንገድ ሊገለፅ የሚችል በመሆኑ ይሄ ነዉ የሚባል የመርሃ ግብር ወሰን የለዉም፡፡ ቢሆንም የስራ ማቆም አድማ ስራን በማቆም፣በማቀዝቀዝና በማቋረጥ አንድን ግብ ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ዓለም ዓቀፍ የስራ ማሕበር (International Labor Organization (ILO) በሰራተኞች መብት ላይ ባደረገዉ ተከታታይ ትግልና ዉትወታ የሥራ ማቆም አድማ እንደ ማሕበራዊ ክስተት ከመቆጠር አልፎ መሰረታዊ ከሚባሉ መብቶች እንዲመደብ አድርጎታል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት እዉቅና በተሰጠዉም የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን ለመደንገግ የወጣው የቃል ኪዳን ሰምምነት (International Covenant on Economic, Social, and Cultural Rights (ICESCR) አንቀጽ 8(1)(d) የስራ ማቆም አድማ በአገራት ሕጎች እዉቅና ሊሰጠዉና ገደቡ እንደ አገራት ሕግ ሊወሰን እንደሚችልም አስቀምጧል፡፡ የሥራ ማቆም አድማዉም የሰራተኞችን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጥያቄዎች እንዲመለስ የሚያደርጉበት ስልትም እንዲሆንና አገራቶችም መብቱን በሕጋቸዉ እንዲያካትቱ ላቅ ያለ አስተዋፅዖ በማድረጉ ብዙ አገሮች ተቀብለዉ የሕጋቸዉ አካል አድርገዉታል፡፡ መብቱም የሚተገበርበት የስራ ዘርፍ ወሰን እንዲኖረዉም ተደርጓል፡፡ ዋና ዓለማዉም የሰራተኛዉ ኑሮ የተሻለ እንዲሆን፣ ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የሰራተኞች ማሕበርና ሕብረት እንዲጠናከርና እንዲበለፅድግ ማድረግ ነዉ፡፡

———
በአገራችንም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ42(1)(ለ) የሰራተኞችን የስራ ማቆም አድማ መብት እዉቅና የሰጠ ሲሆን በአንቀፅ 42(1) (ሀ) የፋብሪካና አገልግሎት ሰራተኞች የስራዉ ባሕሪ የሚፈቅድላቸዉ ሌሎች ሰራተኞች ስራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገልፃል፡፡ በንዑስ አንቀጽ(ሐ) ስራ ማቆም አድማ ማድረግ የሚፈቀድላቸዉ ሰራተኞች በሕግ ሊወስን እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ይህንን ተከትሎም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 የሚተዳደሩ የልማት/ለትርፍ የተቋቋሙ ድርጅት ሰራተኞች ስራ ማቆም አድማ ማድረግ መብት እንዳለቸዉ በአዋጁ አንቀፅ 157 እዉቅና ተሰጥቶታል፡፡በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3(2)(ሠ) በግልጽ እንደተቀመጠዉ በአዋጁ በአንቀጽ 157 የተፈቀደዉ የስራ ማቆም አድማ የማድረግ መብት በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ የጦር ባልደረቦች፣የፖሊስ ሃይል ባልደረቦች፣መንግስት አስተዳደር ሰራተኞች፣የፍርድ ቤት ዳኞችና ዓቃብያነ ሕግ እና ሌሎችን እንደማይመለከት በግልጽ ተቀምጧል፡፡

እስካሁን ባለዉ ሁኔታም ለመንግስት ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ የተፈቀደበት ሁኔታ የለም፡፡ በየፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 2(1) “የመንግሥት ሠራተኛ” ማለት በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ሲሆን “የመንግሥት መሥሪያ ቤት” ማለት ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት እንደሆነ በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 2(3) በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ በመንግስት የሕክምና ተቋም እየሰሩ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎችም ቢሆኑ መስሪያ ቤቱ በመንግስት በጀት የሚተዳደር እንደመሆኑና ሰራተኞችም የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ በመሆናቸዉ የስራ ማቆም አድማ ከተፈቀደላቸዉ ወገኖች አይደሉም፡፡
——
የሕክምና ባለሙያና የስራ ማቆም አድማ!
——
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በሕክምናዉ ዘርፍ የስራ ማቆም አድማ ብዙ ጊዜ የሚገጥም ክስተት አይደለም፡፡ ከ2000 እ.ኤ.አ ወደ ፊት ያለዉን ጊዜ ብንመለከት ለማሳያነት እ.ኤ.አ 2001 በማላዊ የንግስት ኤልዛቤጥ ሆስፒታል የህክምና ባለሙዎች ያደረጉት የስራ ማቆም አድማ እና እ.ኤ.አ 2009 በደቡብ አፍሪካ ጁኒየር ዶክተሮች ያደረጉትን የስራ ማቆም አድማ እናገኛለን፡፡ በሁለቱም አገሮች በተደረጉ አድማዎች በሁለት ጎራ ማለትም አድማዉ መደረጉን የሚደግፉና የሚቃወሙ አስ

ተሳሰቦች ከተለያዩ ወገኖች እተነሱ ሲስተናገዱ ተስተዉለዋል፡፡የተቃርኖዎቹም ዋና ማጠንጠኛ የሕክምና ባለሙያዎች ስራ ማቆም አድማ ማድረግ ከሙያዉ ስነ-ምግባርና ከሕግ አንፃር ይፈቀድላቸዉል ወይስ አይፈቀድላቸዉም፣ በሕክምና ባለሙያዎች መብትና ጥቅም መቅደም አለበት ወይስ የተገልጋዩ ማሕበረሰብ ጤና የማግኘት እና በሕይወት የመኖር መብት የሚሉት ጉዳዮች አከራካሪ ነበሩ፡፡ አሁንም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ተመሳሳይ የሆነ የስራ ማቆምና ማቀዝቀዝ ተግባር በመፈፀሙ በአገራችንም አከራካሪ ሆኖ ሲቅርብ እየተመለከትን ነዉ፡፡ ተቃርኖዎችንም ለመመዘን ከሕክምና ሙያ መሰረተ ሃሳብ መነሳቱ አስፈላጊም ነዉ፡፡
——-
የሕክምና ሙያ የስነ-ምግባር ምንጭ ምንድን ነዉ?
——
ስነ-ምግባር ከሞራል ወይም ከግበረ ገብ እሳቤ በመነሳት የአንድ ሰዉ ድርጊት ትክክል ወይም ስህተት ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን የሚለካ ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሕክምና ሙያ ስነ-ምግባር የስነ-ምግባር መርህ ከሆኑት ዉስጥ ከጥሩና በጎነት (virtue) የሚቀዳ ነዉ፡፡ ጥሩና በጎነት (virtue) ለሰዉ ልጆች ሕይወት መስመርና ቀናነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ባህሪዎችን ሊያላብሱ የሚችሉ ሃቀኝነት፣ ድፍረት፣ አዘኔታ፣ ቸርነት፣ መቻቻል፣ መፋቀር፣ ቅንነት፣ ራስን መግታት፣ ጥበበኝነትን ይዞ መገኘት እንደሆነ ብዙ ፈላስፎች ገልፀዉ አልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ የሕክምና ሙያ ከታማሚዎች ሕይወትን የማዳንና ያለማድን ስራ በመሆኑ የላቀ በጎነትን/ቸርነትን ይጠይቃል፡፡ በጎነት መልካም ባሕሪን በመላበስና በማዳበር የሚመጣ በመሆኑ ከሕግ በላይ ነዉ፡፡

ጥሩ ሕግ መልካም ስነ-ምግባሮችን ሊያካተት የሚችል ቢሆንም ጥሩ ስነ-ምግባር በሌለዉ ማህበረሰብ/ግለሰብ ዉስጥ ሕግ ሊከበር አይችልም፡፡ ከሁሉም በፊት የሚቀድመዉ ስነ-ምግባሩን ተላብሶ መገኘት ነዉ፡፡ ሕጉን/ተጠያቂነቱን ፈርቶ ስነ-ምግባሩን ማክበር ሳይሆን በስነ-ምግባሩ ሕጉን ማክበር ትክክለኛዉ መንገድ ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ ሃኪም ለመሆን ከልቡ የሚያፈልቀዉ የስነ-ምግባር ምንጭ የሆነዉ በጎነት ሊኖረዉ ይገባል፡፡ የሙያዉን ሳይንስ በትምህርት ሊያገኘዉና ሊያሳደገዉ ቢቻለዉም በጎነቱን በትምህርት አያገኘዉም፡፡ በጎነት የሌለዉ ሃኪም ለታማሚዎቹ መድህን ሊሆንም አይችልም፡፡ ስለዚህ የሃኪሞች ድርጊት ዋና መለኪያዉ ሕግን መጣስ አለመጣስ ሳይሆን ከሕግ በላይ የሆነዉን የሙያ መነሻ ስነ-ምግባር አክብሮ መገኘት ነዉ፡፡
——
ሐኪሞች ሙያቸዉንም በተገቢዉ መንገድ እንዲወጡና የሙያዉን ስነ-ምግባር እንዲያከብሩ ለሙያቸዉ ዋና መሪ የሚሆናቸዉን መሓላ (Physician’s (Hippocratic Oath) የተሰኘዉን ቃልኪዳን ይገባሉ፡፡ ምዕራብዓዊያን የሕክምና አባት በማለት በሚጠሩትና ለአሁኑ የሕክምና ሙያ መሰረት በሆነዉ የሂፖክራተስ ቃለ መሓላ የተገልጋያቸዉን ሕይወትና ደህንነት አስቀድመዉ እንደሚሰሩ ቃልኪዳን በማሰር ስራቸዉን የጀምራሉ፡፡ መሓላዉ የሕክምና ባለሙያዎች ባላቸዉ ልዩ ሙያ ተገልጋዮቻቸዉን አስቀድመዉ ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚገልፅ ፍሬ ነገርም አለዉ፡፡ መሓላቸዉ ሕግን ከማክበር ያለፈም ነዉ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች በግል ያላቸዉን መብትና ጥቅም እንዲከበርላቸዉ ሆነ ጤና አጠባበቅ ስርዓቱ እንዲስተካከል ጥያቄም ሲያቀርቡ ከዚህ መሓላቸዉ ፈቀቅ ማለት አይኖርባቸዉም፡፡ የተገልጋያቸዉን ጤና፣ደህንነትና ሕይወት ለመጠበቅና ለማስቀደም ከጅምሩ ቃል ገብተዋልና፡፡
——-
የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማና ፈታኝ ሁነቶች!
—–
አንድ የሕክምና ባለሙያ ሙያዉ የጣለበትን ሃፊነት ለመወጣት ቅድሚያ ተረጋግቶ የሚሰራበት የሥራ ሁኔታ፣ ራሱን ማስተዳደር የሚችልበት በቂ ገንዘብና የሥራ ዋስትና ሊኖረዉ እንደሚገባ የታመነ ነዉ፡፡ ሆኖም መንግስት ለጤና ዘርፉ ሆነ ለባለሙያዉ በሚሰጠዉ አናሳ ትኩረት፣በብልሹ አሰራርና ባለሙያዉን ጫና ዉስጥ በሚያስገባ ግደታ ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎች ቅሬታ ሊፈጥርባቸዉ ይችላል፡፡ ቅሬታቸዉ በጤና ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረዉን ችግርና ከባድ ጫና ተረድቶ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የመንግስት አካል ሲጠፋም ወደ መጨረሻዉ ደረጃ ደርሰዉ ሥራ እስከማቆም ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ስራ ማቆም መፍትሔ ይሆናል አይሆንም፤ መቅድም ያለበት እርዳታ የሚያስፈልገዉ ታማሚ ወይስ የሕክምና ባለሙያዎች ፍላጎት? የሚሉ ፈታኝ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡
——-
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠር ተቃርኖ ሁለት ጫፍ የረገጡ ፍላጎቶችን ወይም ጥቅሞችን ያስተናግዳል፡፡ በአንድ በኩል የጤና ባለሙያዉ የመብት ጥያቄ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተገልጋዩ ማሕበረሰብ ጤናዉ የመጠበቅና በሕይወት የመኖሩ ጉዳይ ፈተና ዉስጥ ይወድቃል፡፡ ተቃርኖዉን ለመፍታት ዋና መለኪያ ሆኖ የሚቀርበዉ የሞራል ጉዳይና የሕክምና ሙያ የቆመበት ስነ-ምግባር መርሕ ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀዉ የሕክምና ባለሙያ ከተገልጋዩ ወይም ከታካሚዉ የቀደመ ነገር ስለሌለዉ የስራ ማቆሙን አድማ ሕጉ ስሚከለክል ሳይሆን ከሕግ በላይ ስለሆነዉ በጎነት ብሎ ለታካሚዉ ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል፡፡

በሌላ መለኪያ የታካሚዉ ወይም የተገልጋዩ ማሕበረሰብ አደጋ ዉስጥ የሚወድቀዉ ጤናዉ ተጠብቆ በሕይወት የመኖር ያለመኖር መብቱ ስለሆነ የዚህን መብት ከሌላዉ ጋር በማወዳደር ይሆናል ፡፡ በሕይወት ከመኖር የቀደም አንዳችም ነገር የለም፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ከሚያነሱት መብትና ጥቅም ጥያቄ ይልቅ ታካሚዎች የሚኖራቸዉ በሕይወት የመኖር መብት ይበልጣል፡፡ የህክምና ባለሙያ የገባዉ ቃልኪዳን አቅሙ በቻለዉ መጠን እስከመጨረሻዉ ደረጃ ታማሚዉን ማገልገል ነዉ፡፡ የገባዉ ቃልኪዳን ከፋኝ ብሎ እርደታ የሚፈልገዉን ሰዉ ከሞት አፋፍ ላይ ጥሎት እንዲጠፋ አያደርገዉም፡፡ በዚህም መሰረት ከሞራል መለኪያ አንፃር ሲታይ የሕክምና ባለሙያዎች በቁስ እረገድ የሚኖራቸዉ ጥያቄ ከታማሚዎች ሕይወት የሚበልጥ አይሆንም፡፡ የሕክምና ሙያ የቆመበትንም መተክል/መርሕ ይንዳል፡፡ የጤና ሥርዓቱ እንዲሻሻልም ለማድረግ የሥራ ማቆም አድማ መፍትሔም አይሆንም፡፡

——–
የሕክምና ባለሙያዎች አድማ የሚያስከትለዉ ዉጤት!
——
የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸዉን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችል ተከታታይና ተደራራቢ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያክል

1ኛ. ክቡር የሆነዉ የሰዉ ልጅ ሕይወት ይጠፋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ባለሙያዎች እ.አ.አ 2009 ባደረጉት የስራ ማቆም አድማ በቂ ሃኪም ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ ታማሚዎች መዳን እየቻሉ ሕይወታቸዉ አልፏል፡፡ እ.ኤ.አ 2001 በ1500 አልጋ ታካሚዎችን የሚያስተናግደዉ የ ማላዊ ንግስት ኤልዛቤጥ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸዉ ሆስፒታሉ እስከመዘጋትና በሆስፒታሉ የነበሩ ታካሚዎች የሚያክማቸዉ ጠፍቶ በበጎ ፈቃደኞች እንደ ቀይ መስቀል ባሉ ድርጅቶች ሕክምናቸዉን እንዲከታተሉ ሁኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባርም የስነ-ምግባር መለኪያ ተደርገዉ ከሚወሰዱት በጎነት(virtue) እና ጠቃሚነት (Principle of Utility) አንፃር ተቀባይነት ያለዉ አይመስልም፡፡

2ኛ. የሕክምና ባለሙያዎች ሥራ በማቆማቸዉ ከታካሚዎቻቸዉ ወይም ተገልጋ ማሕበረሰብ ጋር ያላቸዉ ግንኙነትን ያሻክረዋል፡፡ ተገልጋዩ ወይም ታምሚዉ ጥሎኝ የጠፋ ምኑ አዘኔታ ቢስ ቢሆን ነዉ የሚል አሰተሳሰብ እንዲያዳብር ያደርገዋል፡፡ የአገራችን የሕክምና ባለሙያዎች ተደጋግሞ ከሚነሳባቸዉ ችግሮች አንዱ የመንግስት የሕክምና ተቋሞችን በመተዉና ከሥራቸዉ በመጥፋት በግል የሕክምና ተቋሞች በተሻለ ገንዘብ ይሰራሉ የሚለዉ ነዉ፡፡ የሥራ ማቆሙ አድማም ማሕበረሰቡ በሕክምና ባለሙዎች ላይ ያለዉን አሉታዊ አመለካከት እንዲያጠናክር ያደርገዋል፡፡

3ኛ. አድማዉን ባልተቀላቀሉ የሕክምና ባለሙያዎችና የጤና ተቋሞች ላይ የሥራ ጫና ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለድንገተኛ እና የፅኑ ሕሙማንን የማከም ሥራ እንደማይቆም ተነገረ ቢሆንም እየገቡ የሚሰሩ ባለሙያዎች አድማዉ ሥራቸዉን በሙሉ ልብ እንዳይሰሩና ቸልተኛ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸዉ ይችላል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ችግሩን ለመፍታት ሥራቸዉን ጥለዉ በጠፉት ሐኪሞች ምትክ ከሌላ አገር በዉድ ዋጋ ሐኪሞችን እንዲቀጥርና ሌላ ተደራቢ ችግር ዉስጥ እንዲወድቅ በማድረግ ጫናዉን ያከብደዋል፡፡ የአገር ክብርም ይወድቃል፡፡

———
ከሥራ ማቆም አድማ መልስ ያለዉ አማራጭ!
—–
የሥራ ማቆም አድማ ሥራን በማቀዝቀዝ፣በመለገምና በማቆም የሚገለፅ ቢሆንም የሥራ ማቆ አድማ የመጨረሻ አማራጭ እንደሆነ የዘርፉ አጥኝዎች ይገልጻሉ፡፡ የሥራ ማቆም አድማ ከማድረግ በፊት ቅድሚያ ሌሎች አማራጮችን መፈፀም የግድ ያስፈልጋል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ከስነ-ምግባርና ከሕግ አንጻር የተደገፈ ባይሆንም የሚያነሷቸዉ ጥያቄዎች ሌላ አማራጮችን በመጠቀም ሊመለሱላቸዉ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ብዙ አማራጮችን ማንሳት ቢቻልም በተለያ አገሮች ተሞክሮ ዉጤት ያስገኙትን ለዋቢነት መጥቀስ ይቻላል

አማራጭ አንድ፡- የሙያ ማሕበርን መጠቀምና በተደራዳሪነት ማቅረብ!

እንደሚታወቀዉ የሙያ ማሕበር አንድን ሙያ መሰረት አድርጎ የሚቋቋም እንደመሆኑ ሙያ ማሕበሩ ዋና ዓላማ ሙያዉ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥና የባለሙያዎች መብትና ጥቅም እንዲከበር ማድረግ ነዉ፡፡ የሕክምና ሙያ ማሕበር ባለሙያዎችን በማስተባበር አማራጭ የጤና ፖሊስ እንዲኖርና ችግር ፈቺ ሃሳቦችን በማፍለቅ ከመንግስት ጋር የመደራደር ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ በብዙ አገሮች ተሞክሮ ዉጤት አስገኝቷል፡፡ የሕክምና ሙያ ማሕበር የጤናዉን ዘርፍ መሪ እስኪመስል ድረስ ጉልህ ሚና እንዲኖረዉ ማድረግ ይችላል፡፡ ባለሙያዎችም የሙያ ማሕበራቸዉን አቅም በማጠናከርና ጉልበት በመሆን ዉጤት እንዲያመጣ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በሙያ ማሕበራቸዉ አስተባባሪነት በጤናዉ ዘርፍ እየታየ ያለዉን ችግር ፒቲሽን እስከ ማሰባሰብና ሕዝቡን በማንቀሳቀስ በጤናዉ ዘርፍ እርዳታ ለሚያደርጉ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች፣ለጋሽ አገሮች እንዲሁም በጤናዉ ዘርፍ እየሰራ ለሚገኘዉ የዓለም የጤና ድርጅት ማሳወቅና ጫና መፍጠር ይችላሉ፡፡ በአገራችን የታየዉ ግን የሕክምና ሙያ ማሕበርና ባለሙያዉ በተቃራኒ ጫፍ ሲቆሙና መናበብ እንዳልቻሉ ነዉ፡፡ ባለሙያዎች በራሳቸዉ ተነሳሽነት ሕብረት ፈጥረዉ የሥራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ የሙያ ማሕበራቸዉ በጎን አድማዉን ኮንኖ መግለጫ ሲያወጣ ታይቷል፡፡ ይህ ሚያመላክተዉ ባለሙያዉና የሙያ ማሕበሩ አንድ እንዳልሆነና ባለሙያዎችም የሙያ ማሕበራቸዉን መጠቀም እንዳልቻሉ ነዉ፡፡ ባለሙያዎች የሙያ ማሕበራቸዉን አጠናክረዉ ደግፈዉት ቢሆን ኑሮ ከእነሱ ተቃራኒ የሆነ መግለጫ እስካመዉጣትና ድርጊታቸዉን እስከመኮንን አይደርስም ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ማሕበራቸዉ ሊያመጣ የሚችለዉን ችግር ፈቺ ሃሳብ ተረድተዉ ድጋፍ እንዳላደረጉ መረዳት ይቻላል፡፡
——-
አማራጭ ሁለት፡- የሕክምና ባለሙያዎች ያሉባቸዉን ችግሮች ግልጽና ዓላማዉን ባልሳተ መንገድ ለሕዝብና ለዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ በማሳየት መንግስትን የማሳጣት ስራ በመስራት ሕዝቡና የዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ከጎናቸዉ እንደሆንና በመንግስት ላይ ጫና እንዲያደርግ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሕክምና ባለሙያዎችን እንዲያናግሩ መድረክ የፈጠሩበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ዉይይት አብዛኛዉ የሕብረተሰብ ክፍል ስለጤና ባለሙያዎች ችግርና ስለጤና ስርዓቱ ዉድቀት እንዲረዳ አድርጓል፡፡ አለፍ ሲልም በጤና ባለሙያዎችና በጤና ሥርዓቱ ላይ የገዘፈዉን ችግር የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲታዘብና መንግስት እንዲሳጣ ሰለማዊ ሰልፍ እስከማድረግ ድረስና የዉጪ ሚዲያ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ተግባር በጤናዉ ዘርፍ እርዳታ የሚያደርጉ የዉጪ አገር መንግስታትና ድርጅትን ቀልብ ሊሰብ ስለሚችል መንግስት ሳይወድ በግድ ወደ መፍትሔዉ እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም እቅስቃሴዉ ዓላማዉን እንዳይስትና ከጀርባዉ የፖለቲካ ፍላጎት ግፊት እንዳይኖረዉ መጠንቀቅ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሕክምና ባለሙያዎች በተወሰነ አካባቢ ሰልፍ ቢያደርጉም በአገር ዉስጥ ማሕበራዊ ሚዲያ ተወስኖ ከመቅረትና የአንድ ሰሞን ጫጫታ ከመሆን ያለፈ የዉጪ ሚዲያን ትኩረት ሲስቡ አልታየም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የሕክምና ባለሙያዎች የሚያነሱት ጥያቄ ተጠልፎ የፖለቲካ ጥያቄ የሚመስሉ ነገሮችም እስኪስተዋልበት ድረስ ዓላማዉን ሲስት ታይቷል፡፡
—-
አማራጭ ሶስት፡- ሕዝቡ ሆነ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሕክምና ባለሙያዎች ጥያቄ የመላ ሕብረተሰቡ ጥያቄ እንዲሆን ማድረግና ከሕብረተሰቡ የተወከሉ ትላልቅ ሰዎች ፣የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከትባቸዉ ድርጅቶች የጤና ባለሙያዎችን ወክለዉ ጥያቄያቸዉን ለመንግስት የሚያቀርቡበትና የሚደራደሩበትን ሁኔታ በመፍጠር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡ የማላዊ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕክምና ባለሙያዎችንና መንግስትን ለማድራደር የወሰደዉ እርምጃ ትልቅ ማሳያ መሆን የሚችል ነዉ፡፡
—–
እንደ መዉጫ!

ቀደም ሲል እንደተመለከትነዉ የሕክምና ባለሙያዎች በገዛ ፈቃዳቸዉ ሥራ የሚያቆሙት ተግባር ሙያዉ ከቆመበት ስነ-ምግባር ሆነ ከሕግ አንፃር ተቀባይነት የሌለዉ ከመሆኑ በተጨማሪ የሚፈልጉትን ለዉጥ ማምጣት አይችልም፡፡ ትልቅ ጥያቄ አንስተዉ ጥያቄያቸዉን በሚያሳንስና አጀንዳ በሚያስቀይር መልኩ የአገር መሪን ፎቶ ኤክስ ምልክት አድርጎ ስልፍ መዉጣት ብቻዉን መፍትሔ አያመጣም፡፡ ታማሚን አልጋ ላይ አስተኝቶ ሥራ ማቆም የሚያተርፈዉ በሰዉ ልጅ ሕይወት በመቀለድ ከሕዝቡ መነጠልና መናቅን ነዉ፡፡ ወደ ተጠያቂነቱም ስንመጣ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 421 በግልፅ እንደተቀመጠዉ ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ በእስራትና በገንዘብ ያስቀጣል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችም የገበ ቡትን ቃልና ሕግን በማክበር አርአያ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡

ሲጠቃለል የሕክምና ባለሙያዎች ስለራሳቸዉ መብትና ጥቅም እንዲሁም ስለጤናዉ ዘርፍ መሻሻል ያነሱት ጥያቄ የሚናቅ ባይሆንም እንቅስቃሴያቸዉ ሙያቸዉ የሚጠይቀዉን ስነ-ምግባር እና የገቡትን ቃልኪዳን በሚጥስ መልኩ መደረግ የለበትም፡፡ አንድ የፋብሪካ ሰራተኛ ሥራን በማቀዝቀዝ አድማ ሲያደርግ (በቀን አስር ያመርት የነበረዉን እቃ ወደ አምስት ዝቅ ሲያደርግ) የፋብሪካዉ ምርታማነት ስለሚቀንስ አሰሪዉ ተገዶ ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ ይችላል፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ ሥራዉን በማቀዝቀዝ አድማዉን ገለጸ ማለት ለአንድ ታካሚ ግማሽ ሕክምና እንደ መስጠት ማለት ነዉ፡፡ ይህ ፈፅሞ አይሆንም፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ ቃለ መሓላ ሲፈፅም ሁሉንም ሰዉ/ታማሚ እኩል ሊያገለግል እንጅ ድንገተኛ/ፅኑ ታማሚ ብሎ ሥራዉን ከፋፍሎ ሊሰራ አይደለም፡፡ የሞት አደጋ ያለዉ ድንገተኛና ፅኑ ሕሙማን ክፍል ብቻ አይደለም፡፡ የሕክምና ሙያ የተከበረና ተራዉ ሰዉ ሊኖረዉ ከሚችለዉ በላይ በጎነት፣አዛኝነት፣ቸርነትና ሌላዉን አስቀዳሚ የሆነ ልብ ያለዉ ሰዉ ሊሰራዉ የሚችለዉ ሥራ ነዉ፡፡ ራስን እየጎዱም ቢሆን ሰዉን ሕይወት ማዳን ወደ አምላክነት ጥግ የሚያደርስ ስራ ስለሆነ ስሜታዊነትና ጀብደኝነት በሚንፀባረቅበት መንገድ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ከሕክምና ባለሙያ አይጠበቅም፡፡ ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ተጠቅሞ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረግ እየተቻለ የባሰ ዉጤት የሚያስከትለዉንና ሙያዉን የሚያራክሰዉን መንገድ መምረጥ የጥፋት መንገድ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s