ከዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተቶ ከዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
——————————————

የዎላይታ ሕዝብ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተጎናጸፈውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በሽግግር ወቅት በክልል ዘጠኝ ከተደራጀበት ወደ ደቡብ ክልል ተጨፍልቆ እንዲዋቀር ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እያቀረበ የቆየ ሲሆን በተለይ በ1992 ዓ.ም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብሔሩ ተወላጆች በጥቂት የፓለቲካ ሊህቃን የህዝቡን ማንነት የሚጨፈልቅ ሰዉ ሰራሽ “ወጋጎዳ” የተባለ ቋንቋ በሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው በማምጣታቸዉ አደባባይ ወጥቶ ተቃዉሞ በማድረግ ህዝባዊ ትግል በማድረግ መስዋዕትነት ከፍሎ ህገ መንግስቱ እንዲከበር ፋና ወጊ ሚና በመጫወት ማንነቱን እና ህልውናውን ማስጠበቅ የቻለ እና አሁን የሚገኝበትን የዞን መዋቅር ያገኘ እና የአጎራባች ህዝቦች መብት እንዲከበር ታግሏል:: እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለአንድ መቶ ሃያ አምስት ዓመታት የቆየ ሲሆን ተጨፍልቆ በቆየበት ጊዜ በህገ ወጦች እና ስግብግቦች አማካኝነት በማንነቱ፣ በታሪኩ፣ በባህሉ እና በህልዉናው ላይ የደረሰበትን እና እየደረሰ ያለውን መዋቅራዊ በደል እና ጭቆና ለማስቀረት ሰላማዊ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል:: የዎላይታ ህዝብ ህግ መንግስት ያጎናጸፈውን እራስን በራስ የማስተዳደር እና የራስን ክልል የመመስረት መብቱን መሰረት በማድረግ ከቀበሌ ምክር ቤት እስከ ዞን ምክር ቤት ድረስ በሙሉ ድምጽ አፅድቆ ህዝበ ዉሳኔ እንዲመቻች ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ለክልሉ ም/ቤት ልኮ ምላሽ እየተጠባበቀ ባለበት ባሁኑ ሰዓት የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የዎላይታ ህዝብ እና ሌሎች የክልሉ ህዝቦች ባቀረቡት በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች አስመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉን ሐምሌ 08 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣዉ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ ውሳኔዉ የተድበሰበሰ ከመሆኑ ባሻገር የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በህገመንግስቱ የተረጋገጡ ራስን በራስ የማስተዳዳር መብቶችን እና የብሄሮችን ዕኩልነት በአደባባይ የጣሰ መሆኑን በመገምገም የዎብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከተለዉን ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፡፡

1. የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫዉ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የየራሳቸዉን ክልል የመመስረት ህገ መንግስታዊ መብት ያላቸዉ መሆኑን የሚገነዘብ እንደሆነ የገለፀ ቢሆንም በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ያለዉን ዕኩልነት በሚጣረስ መልክ የዎላይታን ብሔር ጥያቄ በሴራ እና በንቀት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 8፣ 25 ፣39፣ 46 እና 47 ላይ ለብሔር ብሔረሰቦች የተሰጡ መብቶችን የሚጣረስ መግለጫ ያወጣ በመሆኑ ይህ ኢ-ህገ መንግስታዊ እና አምባገነናዊ ውሳኔ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጥብቀን እንገልጻለን፤

2. የዎላይታ ህዝብ የራስን ክልል የመመስረት ህገ መንግስታዊ መብትን መሰረት በማድረግ ከቀበሌ ምክር ቤት እስከ ዞን ምክር ቤት ድረስ በሙሉ ድምጽ አፅድቆ ህዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ወደክልሉ ም/ቤት የላከውን ውሳኔ ለምክር ቤት እንዳይቀርብ ያለ ህጋዊ ሥልጣን ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ በማገድ ላለፉት 8 ወራት ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ በሚል ያረጀ የፖለትካ ድስኩር ማዘግየቱ ከአንድ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተወካይ ነኝ ከሚል የፖለቲካ ድርጅት የማይጠበቅ ኢ-ዴሞክራሲያዊ፣ ኢ-ፍትሐዊ እና ኢ-ሞራላዊ ድርጊት ስለሆነ የዎላይታ ብሔር ጥያቄ በአስቸኳይ ለክልሉ ም/ቤት ቀርቦ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንድያስተላልፍ እየጠየቅን ይህ የማይሆን ከሆነ በህገመንግስቱ አንቀፅ 47 የተቀመጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ እንደተጠናቀቀ የዎላይታ ብሄር ም/ቤት ውሳኔውን በራሱ ለማስፈጽም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ አጥብቀን እናሳስባለን፤

3. ዉድ የሀገራችን ህዝቦች የዎላይታ ሕዝብ በግንቦት ወር፣ 2011 ዓ.ም ባደረገዉ ሠላማዊ ሰልፍ በሀገርቷ እየታየ ያለውን ለውጥ በሚሊዮኖች አደባባይ ወጥቶ መደገፉን የገለፀ ቢሆንም በህገ መንግስቱ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ዕኩል ጥበቃ የተደረገውን መብት ሀገ መንግስቱን በመጣስ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንዱ ብሔረ ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሰረት ህዝበ ውሳኔ ይደረግ፤ ዎላይታ ደግሞ ከሌሎች ጋር ተጨፍሎቆ ማንነቱን በማይገልፀው ደቡብ ክልል ይቀጥል በማለት መወሰኑ በአንድ ሀገር ዉስጥ ሁለት ዓይነት ዜግነት ያለ በማስመሰል የዎላይታ ህዝብ በለውጡ ላይ የሰነቀውን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከህግ አግባብ ውጭ የወሰነዉ ውሳኔ በክልሉ ም/ቤት እና በፌዴራል መንግስት ተቀባይነት እንዳይኖረው እና ውድቅ እንዲደረግ እንጠይቃለን፤

4. ውድ በዎላይታ የምትኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆች: የዎላይታ ብሄር ህገ መንግስታዊ መብቱን በብሔሩ ም/ቤት በሙሉ ድምጽ ወስኖ በሰላማዊ መንገድ ህዝበ ዉሳኔ እንዲመቻች ለክልሉ ም/ቤት ጥያቄ የላከ ቢሆንም በመዘገየቱ መነሻ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ሁላችሁም ሐይማኖትና ብሔር ሳትለዩ በነቂስ ወጥታችሁ በታላቁ ሰላማዊ ሰልፍ በአንድነት የደገፉችሁትን እዉቅና እየሰጠን ከግብ እንዲደረስ አጋሪነታችሁን አጠናክራችሁ እንዲትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

5. ውድ የኢህአደግ ግንባር ድርጅቶች: የዎላይታ ብሔር የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለብሔረ ብሔረሰቦች በዕኩልነት ያጎናጸፈውን ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ታሪካዊ ማንነቱን እና ህልናዉን ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ በብሔሩ ም/ቤት በሙሉ ድምጽ ወስኖ በሰላማዊ መንገድ ህዝበ ዉሳኔ እንዲመቻች ለክልሉ ም/ቤት ጥያቄ የላከዉ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በአንድነት አደባባይ ወጥተዉ የደገፉት ለህገ መንግስታዊ መብት እና ለህግ የበላይነት የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ትግል መሆኑን በመገንዘብ በኢህአዴግ ድርጅታዊ መድረኮች የደኢህዴንን ፀረ ህገ መንግስት እና ኢ-ሞራላዊ የሆነ ዉሳኔ እዉቅና ባለመስጠት እና በማዉገዝ እንድታርሙ እየጠየቅን የዎላይታ ብሔር ጥያቄ ከግብ እንዲደርስ አጋሪነታችሁን ዛሬም አጠናክራችሁ እንዲትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

6. ዉድ የአጎራባች ህዝቦች: የዎላይታ ብሔር የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለብሔረ ብሔረሰቦች በዕኩልነት ያጎናጸፈው ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ታሪካዊ ማንነቱን እና ህልዉናዉን ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ በክልልነት ለመዋቀር የሚያደርገዉ ትግል በሀገራችን የብሔር ብሔረሰቦች ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበርና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚደረግ ዴሞክራሲያዊ ትግል መሆኑን በመገንዘብ የደኢህዴንን ፀረ ህገ መንግስታዊ ውሳኔ እዉቅና ባለመስጠት እና በማዉገዝ ከጎናችን እንድትሆኑ እንጠይቃለን፡፡

7. ዉድ የዎላይታ ብሔር ተወላጅ የሆናችሁ ዲያስፖራዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የላጋዎች፣ የሐይማኖት አባቶች ፣ነጋዴዎች ፣አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሠራተኞች ፣ የግል ባለሁብቶች ሆይ ከቀበሌ ም/ቤት እስከ ዞን ም/ቤት ድረስ በጥሞና መክራችሁ እና በታላቁ ሰላማዊ ሰልፍ በሚሊዮኖች አደባባይ ወጥታችሁ ህልናዉችሁን ለማስጠበቅ በሙሉ ድምጽ ይዉንታ የሰጣችሁን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ አሠራር መሰናክል የገጠመዉ መሆኑን ተገንዝባችሁ ይህንን ለዕኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለህገ መንግስታዊ መብት፣ እና ለህግ የበላይነት የሚታደረጉትን ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ትግል ከማንኛዉም ጊዜ በተሻለ አንድነት እና ህብረት ጥያቄዉ እስኪመለስ ድረስ አጠናክራችሁ እንዲትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

በዴሞክራሲያዊ ትግል የህዝባችንን እጣ ፋንታ ራሳችን እንወስናለን!!

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ
ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s